በቅርቡ መሬት ገዝተው ወይም የሳይት ርክክብ አድርገው ይሆናል። ፕሮጀክትዎን ለማስጀመርም ዝግጁ ኖት።
ሕንፃ ለመገንባት ያሰቡ
ባለሀብት
የቤት እድሳት ለመስራት
የውስጥ ዲዛይነር
የአውራ ጎዳና ስራ ያሸነፈ
ሥራ ተቋራጭ
ትልቅ ፕሮጀክት ለመጀመር ያቀደ
የመንግስት ሃላፊ
እነዚህ ሁሉ ሥራዎች በእቅድ መጀመር አለባቸው። የግንባታ እቅድ ማውጣት በጀትን፣ ጊዜን፣ ሃብትን እና እውቀትን በብቃት ለፕሮጀክትዎ የመመደብ ሂደት ነው።

ዕቅድ ማውጣት ለምን ያስፈልጋል
ግንባታ ማለት የሚፈለጠው ድንጋይ፣ አርማታ ወይም እንጨት ብቻ አይደለም፤ ግንባታ ራዕይ፣ ቅንጅት እና ጊዜ አንድ ላይ ማዋሃድን ያካትታል። በደንብ የተወጠነ ዕቅድ ከሌለ፤ ምርጥ የፕሮጀክት ሀሳቦች እንኳን ወደ መዘግየት፣ በጀት እጥረት እና ማለቂያ ወደሌለው ብስጭት ሊያመሩ ይችላሉ። ዕቅድ ማውጣት: የገንዘብ ችግሮችን ይፈታል፤ የግንባታ ግብዓቶችን፣ መሳሪያዎችን፣ ማሽኖችን እና ሌሎች መሳሪያዎችን አስፈላጊነት ይወስናል፤ በፕሮጀክቱ ሂደት ውስጥ ሊሳሳቱ የሚችሉ ነገሮችን ይተነብያል፤ ጥራት ያለው ግንባታ ያረጋግጣል፤ እና የህግ/የመመሪያ ጉዳዮችን ተፈጻሚነት ያረጋግጣል።
የእርስዎ ሚና እንደ ባለቤት/ፕሮጀክት ሃላፊ
እንደ ባለቤት እና/ወይም የፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ፣ በእርግጠኝነት የእርስዎን ሚና መረዳት እና በእሱ ላይ ማተኮር አለብዎት። የእርስዎ ሥራ መሆን አለበት:
የፕሮጀክቱን ዓላማና ግብ መግለጽ
ጥሩ የመልዕክት ማስተላለፊያ ስልት መዘርጋት
ትክክለኛውን ቡድን ይምረጡ (አርክቴክቶች፣ ተቋራጮች፣ መሐንዲሶች)
የፕሮጀክቱን የገንዘብ ፍላጎት (በጀት) ይወስኑ
የፕሮጀክት የጊዜ ሰሌዳ (መርሃግብር) ያዘጋጁ
እራስዎን እንደ መርከብ ካፒቴን አድርገው ያስቡ - እያንዳንዱን ዝርዝር ነገር አይወስኑም፤ ነገር ግን አጠቃላይ አቅጣጫውን ይዘውራሉ።
የግንባታ ፕሮጀክት 6 ቁልፍ ደረጃዎች
የእቅድዎን ሂደት በግልፅ ለመረዳት 6ቱን የግንባታ ዋና ደረጃዎች ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው። የግንባታ ደረጃዎች ቀለል ያለ ትንታኔ እንደሚከተለው ነው:-
፩. የፕሮጀክት ጽንሰ-ሀሳብ እና ንድፍ

በቀላል አነጋገር፣ ፅንሰ-ሀሳብ ማለት ውጥን ወይም አላማ ሲሆን ንድፍ ደግሞ ፅንሰ-ሀሳቡን በመሳል ወይም በንድፍ ማሳየት ነው። የመሃንዲሶች ቡድን እና ባለቤት/የፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ በአንድ ላይ በመሆን ግልጽ የሆነ የፕሮጀክት ሥራ መጠን እና ንድፍ ማዘጋጀት መቻል አለባቸው።
የበጀት እና የጊዜ ቅድመ ግምት እዚህ ደረጃ ላይ መከናወን ይኖርበታል። ቀጣዩ ደረጃ የባለቤቱን ቁርጠኝነት የሚጠይቅ በመሆኑ የፕሮጀክቱን አዋጭነት በዚህ ደረጃ ላይ መወሰን ያስፈልጋል።
፪. የፕሮጀክት ግዥ
ይህ ደረጃ ፕሮጀክቱን ማን እንደሚያከናውነው ለመምረጥ ይረዳል፤ አማካሪዎች እና ሥራ ተቋራጮች፣ እና ትክክለኛው ሰው/ኩባንያ የቱ እንደሆነ ይወሰናል። የግንባታ አሰራር ዘዴዎች እና ዋጋ በጥንቃቄ መገምገም አለባቸው። የውል ሰነዶች የፕሮጀክቶችን መስፈርቶችን በግልፅ ማስቀመጥ አለባቸው።

ባለቤቱ/የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ለግንባታ ሥራው እና ቁጥጥር የተመረጠውን ሰው/ኩባንያ ማሳወቅ አለበት። ሁለቱም ወገኖች የውል ስምምነቱን መደራደር እና ስምምነቱን ማጠናቀቅ አለባቸው።
፫. የፕሮጀክት ቅድመ-ግንባታ ዝግጅት
ሌላው አስፈላጊ የግንባታ ደረጃ የግንባታ ስራ ከመጀመሩ በፊት ቅድም ዝግጅት ማድረግ ነው፤ ይህ ለሁሉም የፕሮጀክት ተዋናዮች ባለቤቶች፣ የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጆች፣ ተቋራጮች፣ እና አማካሪዎች አስፈላጊ ነው።

እዚህ ደረጃ ላይ ከሚከናወኑት ስራዎች ጥቂቶቹ፡-
- ከተለያዩ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ቢሮዎች ፈቃድ ማግኘት
- የግንባታ ቦታ ቅየሳ (የቦታ ግንዛቤ፣ የመገልገያ መስመሮች፣ ወዘተ.)
- የደህንነት እቅድ
- የፕሮጀክት መርሃ ግብር
፬. ፕሮጀክቱን መገንባት
ግንባታው አሁን ሊጀመር ይችላል። የግንባታ ቡድኑ በተሰጡት ንድፎች መሰረት ሥራውን ይጀምራል። የምህንድስና ሂደቶች ክትትል እና መመዝገብ አለባቸው። የተለያዩ መደበኛ እና መደበኛ ያልሆኑ ስብሰባዎች መደረግ አለባቸው። ለውጦች በውሉ ሰነድ መሠረት መተዳደር አለባቸው።

የግንባታ ግብዓቶች በተቻለ ፍጥነት መቅረብ አለባቸው። ሌሎች አቅርቦቶች፣ የሰው ኃይል፣ እና መሳሪያዎች በጸደቅው መርሃ ግብር መሰረት ወደ ፕሮጀክቱ ማምጣት ያስፈልጋል።
፭. የፕሮጀክት ቁጥጥር

የግንባታ ፕሮጀክት በጣም ብዙ ተንቀሳቃሽ ነገሮች እና በጣም ብዙ ተለዋዋጮች ጉዳዮች ያሉት ሲሆን አእነዚህ ከቁጥጥር ውጭ መሆን የለባቸውም። ሁሉም የበጀት እና የመርሃግብር ስራዎች ክትትል የሚደረግበት ደረጃ ይህ ነው። የሥራውን ጥራት፣ የጊዜ ሰሌዳ እና በጀት በቅርበት በመከታተል ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮች እና አደጋዎችን መቀነስ ያስፈልጋል።
የመዘግየቶች እና የዋጋ ልዩነቶች በአስቸኳይ መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል። የነዚህ ጉዳዮች መከማቸት በወቅቱ ካልተመዘገበ እና መፍትሔ ካልተበጀለት፤ ትልቅ እንቅፋት ይሆናል። ይህን ተከትሎ ማስተካከያ እና እንደገና ስሌቶች መስራት ያስፈልጋል።
፮. ፕሮጀክት መዝጋት
ሁሉም የግንባታ ስራዎች ከተጠናቀቁ በኋላ ፕሮጀክቱን መዝጋት ይቻላል። ይህ ደረጃ የተጠናቀቀው ሥራ ለታቀደለት አላማ መዋል እንደሚችል ያረጋግጣል፤ ክፍያዎችን ማጠናቀቅ እና የፕሮጀክቱ ደረጃዎች መሰነድ ያስፈልጋል።

የተለመዱ ችግሮች ማስወገድ
ልምድ ያላቸው የፕሮጀክት ሃላፊዎች እንኳን ስህተት ይሰራሉ። የሚከተሉትን ስህተቶች ማስተዋል ያስፈልጋል፡
- ያለ ግልጽ እቅድ ወይም በጀት በመጀመር
- የአካባቢ የግንባታ ደንቦችን እና የመንግስት ፈቃዶችን ችላ ማለት
- ዝቅተኛ ዋጋ ያቀረበውን ሥራ ተቋራጭ ወይም አማካሪ መሀንዲስ ያለግምገማ መቅጠር
- በግንባታው አጋማሽ ላይ የንድፍ ለውጦችን ማድረግ (በጣም ውድ ነው!)
- በአቅራቢያው ያሉ መዋቅሮች እና የተቀበሩ መገልገያዎ ች ደህንነት
- የግንባታ ጥራትን ችላ ማለት
የመጨረሻ ሀሳቦች
የግንባታ እቅድ ማውጣት አስቸጋሪ መሆን የለበትም። በትክክለኛ አስተሳሰብ እና መሳሪያዎች፤ ፕሮጀክትዎን በልበ ሙሉነት መምራት ይችላሉ - ምንም እንኳን ለግንባታ መዶሻ ይዘው የማያውቁ ቢሆኑም። ጥያቄዎችን ይጠይቁ፣ ለማወቅ ዝግጁ ይሁኑ እና ያስታውሱ፡ ማንኛውም ትልቅ ግንባታ የሚጀምረው በጠንካራ እቅድ ነው።
ከዚህ በላይ ስላለው ጽሑፍ ምን ያስባሉ?
ከታች ባለው የአስተያየት መስጫ ሳጥን በኩል ሃሳብዎን ያካፍሉ።
ወይም

